ሳይንሳዊ ዘዴ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ሳይንስ ከሌሎች የዕውቀት ዘርፎች (ለምሳሌ ፍልስፍና ወይም ሂሳብ ወይም ስነ ሃይማኖት) የሚለይበት ዋናው ቁም ነገር የሳይንስ ዘዴን በመጠቀሙ ነው። እርግጥ ነው ። ሳይንሳዊ ዘዴ ተብሎ የሚታወቀው ስርዓት ብዙ ጊዜ በዝርዝር ድረጃ በድረጃ በሚከተለው መልኩ ሲቀርብ እናያለን፦
- ስለሚታየው አለም "ጥያቄ" አንሳ። ሁሉም የሳይንስ ስራ የሚጀምረው ጥያቄ በማቅረብ ነው። ትክክለኛና በ"ተመክሮ" ሊመለስ የሚችል ጥያቄ የማቅረብ ችሎታ እንደ ትልቅ የሳይንስ ጥበብ ይቆጠራል።
- ለጥያቄህ መልስ ሊሆን የሚችል "መላ ምት" ፍጠር። "መላ ምት" ማለት የግምት አይነት ሲሆን እንዲሁ በዘፌቀደ የሚደረግ ግምት ሳይሆን ያለፈን ተመክሮ እና ትምህርትን ያገናዘበ ነው። በተረፈ ይህ መላ ምት እውነት ወይም ውሽት መሆኑ ሊረጋገጥ የሚችል መሆን አለበት። ለምሳሌ "ሰማያዊ ቀለም ከቀይ ቀለም የተሻለ ነው" የሚል አስተሳሰብ "ሳይንሳቂ መላ ምት" ሊሆን አይችልም ምክንያቱም እውነት ይሁን ውሽት ማረጋገጥ ስለማይቻል። ነገር ግን ለምሳሌ "ሰማያዊ ቀለምን የሚወድ የሰው ብዛት ቀይ ቀለምን ከሚወደው ይበዛል።" ይህ "ሳይንሳዊ መላምት ሊሆን ይችላል ምክንያቱም እውነት ይሁን ውሸት ሰወችን በመሰብሰብ እና በመጠየቅ በተሞክሮ ማረጋገጥ ይቻላልና።
- መላ ምትህን ሊፈትን የሚችል ሙከራ ዘይድ። እውነተኛ ሳይንሳዊ መላምት በሙከራ ሊፈተን የሚችል ነው። በሙከራ ሊፈተን ካልቻለ በርግጥም ሳይንሳዊ አይደለም። ከዚህ በተረፈ፣ ሙከራው የመላምቱን ውሸትነት ሊያረጋግጥ ይችላል፣ እውነቱነቱን ግን ሊናገርም ላይናገርም ይችላል። ለምሳሌ አንድ መኪና አልነሳ ቢል፣ በሳይንሳዊ መንገድ ጥያቄ መጀመሪያ እናቀርባለን "ለምንድን ነው ያልተነሳው?" መላ ምታችን "ባትሪው ስላለቀ ነው" ይሆናል። ይህን መላምት ለመፈተን የባትሪውን አቅም በቮልት ሜተር እንድንለካ የሙከራ አቅድ እናወጣለን። ባትሪውን ስንለካ ሃይሉ ሳይሟጠጥ ካገኘነው በርግጥም መላምታችን ስህተት መሆኑን በሙከራ አረጋገጥን ማለት ነው። ባትሪው ሃይሉ ተሟጦ ካገኘነው ግን መላምታችን ትክክል መሆኑን አያሳይም ምክንያቱም መኪናው ሌላም ችግር ሊኖርበት ይችላልና። ለምሳሌ "ስታርተሩ" ላይሰራ ይችላል። ስለዚህ ሙከራ አንድን የሳይንስ መላምት ውሽትነት ማረጋገጥ ቢችልም እውነትነቱን ግን አያረጋግጥም።
- ሙከራህን አካሂድ በዚያውም መረጃ ሰብስብ።
- ከሙከራህ ተነስተህ ድምዳሜ ላይ ድረስ። በርግጥ ያቀረብከው መላምት ውሽት መሆኑን ሙከራህ ያሳያል? ካላሳየ መላምትህ ለጊዜው (በሌላ ሙከራ እስካልተስባበለ ድረስ) ልክ ነው ማለት ነው። ውሽት መሆንኑን ካረጋገጥክ ከጀረጃ 2 ጀምረህ እንደገና ሞክር።
- ድምዳሜህንና መላምትህን ለሌሎች አስታውቅ። ይህ ደረጃ ሳይንቲስቶች የጋን መብራት እንዳይሆኑ ከማገዱም በላይ ያንድን ሰው መላምቶችና ተመክሮወች በሌሎች ሳይንቲስቶች እንዲመዘን እና እንዲረጋገጥ መንገድ ይከፍታል።
እነዚህ እርከኖች በርግጥ ሁልጊዜ በሁሉ ሳይንቲስት የሚደረጉ ባይሆን፣ ነገር ግን ባጠቃላይ መልኩ ስለዓለማችን አስተማማኝ ሃቆችን ለማግኘት የሚረዱ መሆናቸው ይታመንባቸዋል።