መኮንን እንዳልካቸው
From Wikipedia, the free encyclopedia
ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው፤ አርበኛ፣ ስደተኛ፣ የውጭ ጉዳይ አደራዳሪ፣ ታላቅ ደራሲና በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
መኮንን እንዳልካቸው የካቲት ፲ ቀን ፲፰፻፹፫ ዓ/ም ከአባታቸው ከባላምባራስ እንዳልካቸው አብርቄ እና ከናታቸው ከወይዘሮ አቦነሽ ተክለ ማርያም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ተጉለት፣ አዲስጌ ላይ ተወለዱ።
ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ካርቱም ከሚገኘው የሶባት የጦር መኮንኖች ትምህርት ቤት ተመርቀዋል። በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሳሉ የትምህርት አቻዎቻቸው እነ ልጅ ተፈሪ መኮንን እና ልጅ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ።
ልጅ መኮንን እንዳልካቸው “የሕልም ሩጫ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የጀመረው የሥልጣን እርምጃቸው የልጅ ኢያሱ ሞግዚት እና እንደራሴ የነበሩት አጎታቸው፣ ራስ ተሰማ ናደው ካረፉ በኋላ በተለያዩ ባለ ሥልጣናት እንደተገታ አሥፍረውልናል።