1 አመነምሃት
From Wikipedia, the free encyclopedia
ሰኸተፒብሬ 1 አመነምሃት ግብጽን በመካከለኛ መንግሥት (12ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ2002 እስከ 1972 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የ4 መንቱሆተፕ (ነብታዊሬ) ተከታይ ነበር።
አመነምሃት መጀመርያ በነብታዊሬ አጭር ዘመን የነብታዊሬ አለቃ ወይም ሚኒስትር ይመስላል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህ አመነምሃት እራሱ ፈርዖን ሆነ። ነብታዊሬ ወዴት እንደ ሄደ ወይም እንደ ኖረ እንዳልኖረ አይታወቅም።
አመነምሃት ከ፯ መቶ ያህል ዓመት በፊት ጠፍቶ የነበረውን ጥንታዊ መንግሥት ለማሳደስ ያደረገው ጥረት ሊታወቅ ችሏል። ይህም በጥንታዊ መንግሥት ፈሊጥ የሆነውን ሀረም በማስገንባቱ በኩል ይታያል። እንዲሁም ከአመነምሃት ዘመን በግብጽኛ የተጻፈው ሥነ ጽሁፍ ይህን ሀሣብ ያስረዳል። ከነዚህ መካከል የአመነምሃት ትምህርት፣ የሲኑሄ ታሪክ እና የነፈርቲ ትንቢት ዋናዎቹ ናቸው።
በአመነምሃት ዘመነ መንግሥት በ፳ኛው ዓመት (1982 ዓክልበ. ግድም) ልጁን 1 ሰኑስረትን ከእርሱ ጋር በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ አስነሣው። በዚህ ዓመት ደግሞ የግብጽ ዋና ከተማ ከጤቤስ ወደ አዲስ ከተማ ኢጭታዊ አዛወረው። በ፳፱ኛው ዓመት ዋዋት (ስሜን ኩሽ መንግሥት) እንደ ያዘ ከአንድ ጽላት ታውቋል።[1]
በጽሑፎቹ መሠረት ልጁ ሰኑስረት በሊብያ እየዘመተ አመነምሃት በሤራ እንደ ተገደለ ይታሥባል።