የኡር-ናሙ ሕግጋት
From Wikipedia, the free encyclopedia
የኡር-ናሙ ሕገጋት እስከ ዛሬ ከተገኙት መንግሥታዊ ሕግ ሰነዶች መኃል ከሁሉ ጥንታዊ የሆነው ሰነድ ነው። ሰነዱ የተጻፈው ከክርስቶስ ልደት ከ1983 ዓመት በፊት (ኡልትራ አጭር) በሱመርኛ ቋንቋ ነበር። በመቅደሙ የኡር ንጉሥ ኡር-ናሙ ስም ቢጠቀስም አንዳንድ ሊቃውንት ግን ምናልባት የልጁ የሹልጊ ሥራ ይሆናል ብለው ያምናሉ።
መጀመርያ የተገኘው ቅጂ በተሰበረ ጽላት በኒፑር ፍርስራሽ ሲሆን፣ በ1944 ዓ.ም. ሊቅ ሳሙኤል ክሬመር አስተረጎሙት። ሆኖም ሰባራ ክፍሎች እንደ መሆኑ ከሕጎቹ ሁሉ 5ቱ ብቻ ሊታነቡ ይችሉ ነበር። ዳሩ ግን ሌሎች ቅጂዎች በኡርና በሲፓር ከተገኙ በኋላ አሁን ከ57 ድንጋጌዎች በጠቅላላ፣ 40 ያሕል ሊታወቁ ተቻለ።
የኡር-ናሙ ሕገጋት ከሃሙራቢ ሕጎች በ300 አመት አስቀደሙ። ሆኖም ሌሎች የሕገጋት ሰነዶች ከኡር-ናሙ ጊዜ በፊት በሱመር እንደ ኖሩ ይታወቃል። የላጋሽ ንጉሥ ኡሩካጊና የሕግ ማሻሻል እንዳወጣ የሚል ጽላት ተገኝቷልና።
በዚህ ሰነድ ሕጎቹ «አንድ ሰው እንዲህ ቢያደርግ፣ እንዲህ ይደረግ» በሚመስል አባባል ይጻፋሉ። ይህም ዘዴ ደግሞ በኋለኛ ሕገ መንግሥታት ይታያል። ከንጉሡ («ሉ-ጋል» ወይም ታላቅ ሰው) በታች፣ ከኅብረተሠቡ 2 አይነት ማእረግ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም፦ 1) «ሉ» ወይም ነጻ ሰው እና 2) «አራድ» (ባርያ) / «ጌሜ» (ገረድ) ናቸው። የ«ሉ» ወንድ ልጅ ሚስት እስከሚያገባ ድረስ «ዱሙ-ኒታ» ይባል ነበር። የሴት («ሙኑስ») ሁኔታ ከሴት ልጅ («ዱሙ-ሚ») ጀመሮ እስከ ሚስት («ዳም») ከዚያም ከባሏ እረፍት ብትኖር ኖሮ እስከ ጋለሞታ («ኑማሱ») ድረስ ይደርስ ነበር።
- ደግሞ ይዩ፦ የሕገ መንግሥት ታሪክ።